እንደምን ነሽ? እንደምን ነህ? እስቲ ቅዳሜን እናፍካው! የፀዳ ቀደዳ ነው ጌታዬ!
.
“ህዝብ ነው መሪን መምራት ያለበት?” ወይስ “መሪ ነው ህዝብን መምራት ያለበት?” የሚለው ፍልስፍና አወዛጋቢ ነው። እሱ ግን “መሪ ነው ህዝብን መምራት ያለበት!” የሚለውን መንገድ ተከትሏል!
ምን መሰለህ!
“Russia” የምትባል ሃገር ስትሰማ ስለ “Vodka”፣ “በረዶ”፣ “ፀጉራም ድቦች”፣ “ጥንታዊ ህንፃዎች እና ካቴድራሎች” ወይም “ወፍራም የብርድ ካፖርት አድርገው ሲጃራ ስለሚያጨሱ እና ብዙም ስማይስቁ ሰዎች” ብቻ ካሰብክ ተሳስተሃል!
ብዙ ድህነት፣ ብዙ ሞት፣ ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ጦርነት፣ ብዙ ስቃይ፣ ብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ከፍታ እና ዝቅታዎችን ያየች ሃገር ናት። እንደዛ ዓለምን ያንቀጠቀጠችው “Soviet Union(ሶቭየት ህብረት)” እ.ኤ.አ 1991 ላይ ፈረሰች፣ ተበታተነች! ከአሜሪካ ጋር የነበረው ቀዝቃዛው ጦርነትም በተመሳሳይ ወቅት መቋጫውን አገኘ። ተከፍሎ በማያልቅ እዳ እና መሪዎች በተፈራረቁ ቁጥር በሚለኮሱ ጦርነቶች የተማረረው ህዝብ “ነገ ማን መጥቶ ይመራን ይሆን?” ብሎ በተስፋ እና በስጋት መጠበቅ ጀመረ!
.
ይህ ሰው እጅግ ደሃ ከሚባሉ ቤተሰቦች ተወለደ! ሁለት ታላላቅ ወንድሞቹ ሞቱ! አባቱ በጦርነት የቆሰለ ነው። እናቱ ምስኪን የፋብሪካ ቀን ሰራተኛ ነበረች! እጅግ ጠባብ ቤት ውስጥ ከአይጥ ጋር እየተባረረ ኖረ! ዛሬ ላይ “…አደን እንዴት ልትወድ ቻልክ?…” ተብሎ ሲጠየቅ “..ልጅ እያለው ቆሻሻ ቤት ውስጥ እኖር ስለነበረ ብዙ አይጦች ነበሩ! እነሱን እያባረሩ መግደል እወድ ነበር! ከዛን ግዜ ጀምሮ ያዳበርኩት ልምድ ነው!…” ይላል!
በመጨረሻም ጎርምሶ የህግ ትምህርቱን አጠናቆ ተመረቀ! ጠበቃ መሆንን ግን አልመረጠም! ቀጥታ ወደ ሃገሪቱ ስለላ ተቋም ወደሆነው አስፈሪው “KGB” ገባ! የስለላን ጥበብ ከስር መሰረቱ ተማረ! የዓለማችን ድንቅ መሪ እንዴት መሆን እንደሚችል ብዙ አነበበ፣ አጠና፣ የብዙ መሪዎችን አካሄድም በደንብ መረመረ!
በ 16 ዓመት የስለላ ሙያ ቆይታው ከባድ የሚባለውን የጀርመንኛ ቋንቋን ተምሮ አቀላጥፎ መናገር ቻለ! የሌተናል ኮሎኔን ማዕረግንም አገኘ! በስለላ ስራው ወደተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በድብቅ እየሄደ ብሩህ ጭንቅላት ያላቸውን ወጣቶች ለ “KGB” እንዲመለመሉ ያደረግም ነበር። ቀስ ብሎ የሃገሪቷ የደህንነት ካውንስል ዋና ፀሃፊ ሆነ! ስናሳጥረው እ.ኤ.አ 2000 ላይ የ “Russia” ፕሬዝዳንት ሆነ!
ጌታዬ! ዝም ብለህ አስበው! ከ ቆረቆዘ ደህንነት እና አይጥ አዳኝነት ወደ ሰላይነት ከሰላይነት ወደ ዓለማችን ትልቋ ሃገር ፕሬዝዳንትነት ነው የተረማመደው!
ማን?
“Vladimir Vladimirovich Putin!”
አስፈሪ ነው። ፊቱ አይፈታም። ግርማ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው። አይደለም ለማዋራት አጠገቡ ለመቆም እንኳን ብዙ መሪዎች ይንቀጠቀጣሉ። ፀዴ ነው፣ ፈርጣማ ነው፣ የወንዳወንድነት ጥግ ነው፣ ካሬዝማው ገዳይ ነው፣ እንደሌሎቹ መሪዎች የተዝረከረከ ቦርጫም ሳይሆን ስፖርተኛ ነው፣ በጁዶ ስፖርት ስምንተኛ ዳን ላይ ደርሷል! ወደ ስልጣን ሲመጣ ተበታትና፣ ከነበረችበት ከፍታ ወርዳ፣ እዳ በእዳ ሆና እና የህዝቦቿ ስነ ልቦና ላሽቆ ዘጠኝ ዓመታት ከተቆጠሩ በኃላ ነው! ቤተ መንግስት ሲገባ ብዙም ሰው አያውቀውም! ስልጣን በመያዙ ደስተኛ የነበረውም የህዝብ ቁጥር 2% የሚሆነው ብቻ ነበር!
ወደ ስራ ገባ!
ከፍተኛ የ “policy” ማሻሻያዎችን አደረገ! ሃገሪቷን ከዓለማችን ዋነኛ የነዳጅ አምራች ሃገሮች ተርታ አሰለፋት፣ 70% የሚሆነው ህዝብ መካከለኛ ገቢ ያለው ሆነ፣ ኢንቨስትመቱን ለማበረታታት ታክስ በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ፣ የህዝቡ የመግዛት አቅም ጨመረ፣ የሃገሪቷ ዋና ከተማ “Moscow” የዓለማችን ቁጥር አንድ ብዙ ቢልየነሮች መገኛ ሆነች፣ የሃገሪቱን የ “Nuclear” አቅም አሳድጎ “Russia” የዓለማችን ቁጥር አንድ የ “Nuclear” ክምችት ያላት ሃገር እንድትሆን አደረገ፣ የሃገሪቷ አጠቃላይ “GDP” ወደ 4 ትሪልዮን ዶላር ደረሰ፣ የህዝቡ የነብስ ወከፍ ገቢ 28 ሺህ ዶላር አለፈ፣ በአውሮፓ አንደኛ እና በዓለም ሁለተኛ መሆን የቻለ የሃገር መከላከያን ገነባ። የሃገሪቷ ስራ አጥ ቁጥር 4.5% ብቻ ሆነ፣ “Russia” ከዛ ሁሉ እዳ ወጥታ የዓለማችን ትንሹ የውጪ ሃገር እዳ ያለባት ሃገር መሆን ቻለች! ለሶስት ተከታታይ አመታት በ “Forbes” ጋዜጣ የዓለማችን ተፅህኖ ፈጣሪ ሰው መሆን ቻለ! እሱ ወደ ስልጣን ሲመጣ ደስተኛ የነበረውን 2% ህዝብ ወደ 86% ማድረስ ቻለ። ህዝቡ ስለ “Putin” ሲናገር “….ሃገር ወዳድ ነው! ለሃገሩ ሟች ነው! ክብራችንን የመለሰው እሱ ነው! የሃገር ፍቅራችንን የጨመረው እሱ ነው! አብዛኛው ራሽያዊ በሱ ምክንያት ለሃገሩ ለመሞት ዝግጁ እንዲሆን ሆኗል! የምዕራባውያኑን ተፅህኖ መቋቋም ችሏል! ክብራችንን መልሷል!….” ይላሉ!
የሰውየው ስብዕና ገራሚ እና አወዛጋቢ ነው። ሲፈልግ ባህር ውስጥ ሰምጦ ከዶልፊኖች ጋር ሲዋኝ ታገኘዋለህ። ሲያሻው ጫካ ገብቶ እንስሳት ሲያድን እና አሳ ሲያጠምድ ልታየው ትችላለህ! ደስ ሲለው ራቁቱን ፈረስ ይጋልባል! የበጎ አድራጎት መድረኮች ላይ ሄዶ በዛ አስፈሪ ካሬዝማው ጠብሰቅ ያለ ንግግር ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ ለታዳሚያን ፒያኖ እየተጫወተ ሲዘፍን ታየዋለህ! ስለ ግል ህይወቱ ማንም አያውቅም! ከተፋታት ሚስቱ የወለዳቸው ሁለት ሴት ልጆቹ የት እንደሚኖሩ አይታወቅም! የኮሌጅ ትምህርታቸው ሳይቀር በ “Fake” ስም እና ማንነት ተምረው እዛው “Russia” ውስጥ ማንም ሳያውቃቸው እንደጨረሱ ይነገራል! ስብሰባዎች ላይ ሁሌ ከተባለው ሰዓት አርፍዶ ይመጣል! የእንግሊዟን ንግስት እና የካቶሊኩን ጳጳስ ሳይቀር ከአንድ ሰዓት በላይ አስጠብቋቸው ወደ ስብሰባ የመጣ ደፋር ሰው ነው። ሰላይ እንገናኝ የተባለበት ሰዓት አናቷ ላይ አይመጣም! በዛች ሰዓት ምን እንደተጠነሰሰለት አይታወቅማ ጌታዬ!
ሰውየው ያለውን ያደርጋል፣ ያቀደውን ያሳካል! እሱ ካስቀመጣት መስመር አንዲት ኢንች ውልፊት ማለት አይቻልም! ህዝቡን ይመራል እንጂ ህዝብ አይመራውም!
“….የመንግስት ሃላፊነት የህዝቡ መጠጫ ብርጭቆ ውስጥ ማር ማንቆርቆር ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም የሚመር መድሃኒት መክተትን ይጨምራል!…” ይላል!
ሃሜቶች፣ ወቀሳዎች እና አንዳንድ ጥሬ ሃቆች!
የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም እኛ በሚድያ የሚነገሩን ሰዎች ሳይሆኑ “Vladimir Putin” ነው ይባላል! ጠቅላላ ሃብቱ ወደ 200 ቢልዮን ዶላር ገደማ ይደርሳል ይላሉ።
የሃገሪቱ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ትልቁ ድርሻ የሱ ነው ይባላል! 20 እጅግ ቅንጡ እና በወርቅ የተንቆጠቆጡ ቤተ መንግስቶች፣ አራት የግል ጀልባዎች ፣ 58 የግል ጀቶች፣ 700 የሚሆኑ ውድ ውድ መኪኖች እና ወደ አንድ ሚልዮን ዶላር የሚያወጡ የእጅ ሰዓቶች አሉት ይባላል! እሱ ግን “….የስራዬ ደሞዝ በአመት 133 ሺህ ዶላር ብቻ ነው! የሚያወሩት ሁሉ ውሸት ነው!…” ይላል!
በሃገሪቱ ያሉ ሚድያዎች ሰውየውንም ሆነ መንግስቱን በጭራሽ መተቸት አይችሉም! እዛች ሃገር መንግስትን እየተቃወሙ በህይወት መኖር ዘበት ነው! የሆነ ቀን ላይ ከየት እንደተተኮሰ የማታወቀ “Sniper” ግንባርህን ብሎ ይደፋሃል! በዚህ ምክንያት ብዙ ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ ተገለዋል፣ ተሰደዋል! ብዙ ለሃገሪቱ መንግስት ይሰሩ የነበሩ ሰላዮች ወደ ተለያዩ ሃገራት ተሰደው እንኳን መኖር አልቻሉም። የሃገር ሚስጥር ይዘህ ወዴት ወዴት ጌታዬ! በማታውቀው መንገድ ወይ የምትጠጣው ሻይ ውስጥ ወይ የሆነ ቦታ የበላኸው ምግብ ውስጥ አደገኛ መርዝ ተደርጎበት ትሞታለህ! ሰውየው የሚያስገድልህ እጅግ በረቀቀ መንገድ ነው! “Radioactive” ሳይቀር ሊለቅንህ ይችላል!
ብዙ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ ፖለቲከኞች እና ተቃዋሚዎች ሳይቀር እጅግ ቀዝቃዛ ወደሆነው “Siberia” ውስጥ የሚገኝ እስር ቤት ተወርውረው ፍዳቸውን እየበሉ ነው ይባላል!
ሰውየው የፈለገውን ነገር እንደሚያደርግ የምታውቀው “የሃገሪቷ ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን ሁለት ተርም ብቻ ነው!” የሚለውን ህግ አሻሽሎ ለአራት ተርም አድርጎታል! ከዛም አልፎ ” Referendum” በማድረግ እድሜ ልክ ለመምራት ተፍ ተፍ እያለ ነው! ኸረ እንደውም በቅርቡ የሃገሪቷ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እድሜ ልክ ያለመከሰስ መብትም አፅድቋል! ጌታዬ አሜሪካን የምታክል ልዕለ ሃያል ሃገር ምርጫ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የፈለገውን ሰው ነጩ ቤተ መንግሥት ውስጥ ማስቀመጥ ችሏል ተብሎ ይታማም አልነበር እንዴ?
ስናጠቃልለው!
“Putin” በብዙ መለኪያዎች እጅግ በጣም ከባድ ሰው ነው!
መልካም ምሽት! መልካም ቅዳሜ!