ምን መሰለህ ጌታዬ!
በፍንዳታነት ዘመናችን ቢያንስ የሱን አንድ መፅሃፍ አንብበናል! ቤተሰቦቻችን “….ልጅሽ የዚህን ሰውዬ መፅሃፍ ካነበበማ አበደ!…” ተብለዋል። መፅሃፎቹ የአንድ ሰሞን መነጋገርያ ሆነው ጉድ ተብሏል! አንዳንዶች የህይወት ፍልስፍናው በደንብ ገብቷቸው ይሁን ስሜታዊ ሆነው አምርረው ተከትለውታል። አንዳንዶች እውነትም በሰውየው መፅሃፎች ይሁን በሌላ ምክንያት እንደተፈራው ጨልለው አይተናል። አንዳንዶች ደግሞ የሰውየውን መፅሃፍቶች እንደማንኛውም መፅሃፍ አንብበው የሚወሰደውን ወስደው፣ ያላመኑበትን ደግሞ ጥለው ወደ መፅሃፍ ሼልፋቸው መልሰውታል፣ ወይ ለሰው አውሰውታል ወይ ደግሞ በኪሎ ለስኳር መጠቅለያነት በ 2 ብር ሸጠውታል። ለማንኛውም በዚህ ሰውዬ ስም የወጡ እስከ 680 መፅሃፎች ገደማ እንዳሉ ይነገራል! ነገር ግን ሰውየው “….እኔ አንድም መፅሃፍ አልፃፍኩም! ነገር ግን ከ 100 ሺህ በላይ መፅሃፍትን አንብቤያለሁ! በቀን ውስጥ ቢያንስ ከስድስት ያላነሱ መፅሃፍትን እጨርስ ነበር!”.. ይላል! ” ባቡጁ ምን አነበበ!”
ለማንኛውም ሰውየው በትክክለኛ ስሙ “Acharya Rajneesh Bhagwan” ይባላል! አብዛኛዎቻችን የምናውቀው “Osho” በተሰኘው ስሙ ነው።
“Osho” የ 20ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ አነጋጋሪ ሰው ነው! በትንሹ ከ 500,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ሁሉንም ነገራቸውን ጥለው ተከትለውታል። የንግግር ጥበብን በሚገባ የተካነ፣ የብዙዎችን የህይወት ፍልስፍና የቀየረ፣ ተከታዮቹ ገና ሲያዩት እራሳቸውን ስተው የሚወድቁለት፣የሚንዘፈዘፉለት፣ አቅላቸውን የሚስቱለት እና በሱ እጅ መዳሰስን ገነት የመግባት ያህል የሚቆጥሩለት ምትሃተኛ ሰው ነበር።
አንቺም እኔም ግን የማናውቀው ለዚህ ሰውዬ እዚህ መድረስም መውደቅም ትልቁን አስተዋፅኦ ያበረከተች አንዲት ገራሚ ሴት አለች!
ወደ እርሷ መጣሁ! ቆይ አንዴ አባዬ!
.
.
.
“Osho” የተወለደው አንዲት ትንሽዬ የህንድ መንደር ውስጥ ነው! በአያቶቹ እጅ የፈለገውን እንዲያስብ፣ የፈለገውን እንዲያወራ እና የፈለገውን እንዲያደርግ እየተነገረው ያደገ ቅምጥል ልጅ ነው። ትምህርት ቤት ውስጥ ገና በልጅነቱ እኔ ነኝ ያለ ጎበዝ ተከራካሪ ነበር! መምህሮቹን ሳይቀር በክርክር ያሸንፍ እና ያሸማቅቅ ጭምር ነበር። ዩኒቨርሲቲ ይገባና በፍልስፍና ዲግሪውን ይሰራል! ከዛም አባዬ እራሱን እንደ ነብይ ማየት ጀመረአ። ወደ ተለያዩ የህንድ ከተሞች እየዞረ የህይወት ፍልስፍናውን ያስተምር፣ ያስረዳ፣ በሰዎች ዘንድም ያሰርፅ ተያያዘ። ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ቻለ! የህይወት ፍልስፍናው “አዲስ የሰው ልጅ ማንነትን” መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው። እሱ “Enlightenment” ይለዋል! የሰው ልጅ ጥልቅ ሃይል እንዳለው፣ በራሱ መንገድ እውነትን ፈልጎ ማግኘት እንደሚገባው፣ በነፃነት መኖር እና ፍቅርን በነፃ ሰጥቶ መቀበል እንዳለበት ያምናል፣ ያስተምራል።
ወሲብ ነፃ መሆን እንዳለበት እና አንድ ሰው ካሻው ከማንኛው ሰው ጋር መመቻቸት እንዳለበት ያምናል። “ትዳር” የሚባል ተቋም በጭራሽ እንደማያስፈልግም ያስተምራል። ብችል “ትዳር” የሚባለው ተቋም ከምድረ ገፅ ባጠፋው ደስ ይለኛል ይላል! አብዛኛዎቹ የዓለማችን ችግሮች የሚመነጩት ትዳር ከሚባል ቆሻሻ ተቋም ነው ብሎ ሽንጡን ገትሮም ይከራከራል! “Meditation” እና “Therapy” የሰው ልጆች ቁልፍ መዳኛ መንገዶች እንደሆኑም ያምናል! ጌታዬ! የመጣሁት ስለ ሰውየው የህይወት ፍልስፍና ልክነት አልያም ስህተት ልነግር አይደለም!
ምን ሆነ መሰለህ!
ትዳር የመረራቸው፣ የከተማ ህይወት ያስጠላቸው፣ የመኪና ጡሩንባ የሰለቻቸው፣ ስራ በዝቶባቸው ጭንቀት ውስጥ የገቡ እና የተለያዩ የግል ችግሮች ያሉባቸው አሜሪካውያን እና አውሮፓውያን ሁሉንም ነገር ጥለው ወደ ህንድ መጉረፍ ጀመሩ!
ለምን?
የ “Osho”ን ትምህርት እየተማሩ ቀሪውን ህይወታቸውን ለማሳለፍ! ተራ ሰዎች አይደሉም! ጠበቆች፣ ኢንጅነሮች፣ ደራሲያን፣ መምህራን፣ ቱጃሮች፣ አርክቴክቶች፣ ጋዜጠኞች…ብቻ ምን አለፋህ ሁሉም የ “Osho” እግር ስር መጥተው ተደፉ! እሱም እጁን ግንባራቸውን ላይ ጭኖ ፀለየላቸው! መሬት ላይም ተንፈራፈሩ፣ በመዳን ስሜትም ብርጭቆ ብርጭቆ የሚያክል እንባ አነቡ!
በዚህ መሃል ከሰውየው ቅልጥ ያለ ፍቅር ይዧት አንዲት ሴት መጣች። “Sheela” ትባላለች። በትውልድ ህንዳዊት ናት! ለሷም ፀለየላት፣ “Meditate” አስደረጋት፣ የህይወት ፍልስፍናውን አስተማራት። እሷ ግን በነዚህ ነገሮች ብዙም አልተመሰጠችም። ሰውየው ያለውን አቅም “ዓለም አቀፋዊ” እንዲያደርገው ፈለገች። ቀስ በቀስ “የግል ፀሃፊው” ሆነች። በመካከላቸው ያለው ግንኙነት እየጠበቀ መሄድ ሲጀምር “ቃል አቀባዩ” ጭምር መሆን ቻለች። ሰውየው ህንዳውያን እንደ ነፃነት አባት የሚያዩትን “Ghandi”ን ይተች ነበር፣ የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንንም ክፉኛ ያጣጥል ነበር! የሰውየው የህይወት ፍልስፍና በወቅቱ ከነበረው የህንድ መንግስት ጋርም ብዙ ሰጣ ገባ ውስጥ እየከተተው ስለነበር ደህንነቱ አሳሳቢ ሆነ!
“Sheela” እንዲህ አለችው!
“…….ለምን ወደ ነፃነቷ ምድር “አሜሪካ” አንሄድም? ለምን “አሜሪካ” ውስጥ ሰፊ መሬት ገዝተን የራሳችንን የተቀደሰች ከተማ አንገነባም? ፍቅር፣ ርህራሄ እና መካፈል የበዛባት ማንም የምንም ነገር ባለቤት የማይሆንባት፣ ስግብግብነት ፅዩፍ የሆነባት፣ ፍፁም ቁጡ እና የተናደዱ ሰዎች የማይኖሩባት የቃል ኪዳን ከተማን አንገነባም? መብት፣ ዴሞክራሲ፣ መደራጀት፣ በነፃነት መምረጥ፣ እምነትን እንደልብ ማራመድ የምትፈቅደው አሜሪካ ናት! እዛ እንሂድ!…” ብላ መከረችው! ተስማሙ!
በአሜሪካ “Oregon” ግዛት “Antelope” የምትባል መንደር ውስጥ 64 ሺህ ሄክታር መሬት ገዙ! ከተማዋ ውስጥ የሚኖሩት ከ 150 የማይበልጡ እድሜያቸው የገፋ እና ጡረታ የወጡ ምስኪን አዛውንቶች ነበሩ!
ከዛስ?
አብዛኛዎቹ የ “Osho” ፍልስፍና ተከታዮች የተማሩ እና ብልጥ ስለነበሩ ከተማዋን ለመገንባት ብዙ ግዜ አልፈጀባቸውም። የሰውየው “ቃል አቀባይ” የሆነችው “Sheela” “Osho”ን ለመከተል የመጡትን ባለሃብቶች፣ ኮንትራክተሮች እና አርክቴክቶች አሰባስባ ያለመችውን ከተማ አስገነባቻቸው። የከተማዋን ስምም የ” Rajneesh ከተማ” አሏት። የሰውየው ተከታዮች በሙሉ ብርቱካናማ ቱታ ልብስ እንዲለብሱ ተደረገ። ቀስ በቀስ የራሳቸውን ሱቆች፣ የራሳቸውን ባንክ፣ የራሳቸውን ልብስ ቤቶች፣ አስር ሺህ ህዝብ የሚይዝ የማምለኪያ አዳራሽ፣ የራሳቸውን አየር ማረፊያ፣ ግድብ፣ አውሮፕላኖች፣ ግዙፍ ዘመናዊ እርሻዎች፣ እንስሳት ማርቢያዎች እና ሰው ሰራሽ ሃይቆች ሳይቀር ሰሩ! ልብ በል ጌታዬ! ይህንን ሁላ የምታሳልጠው፣ የምታሰራው፣ የምትቆጣጠረው ይችህ ሴት ነች! የ “Osho” ዋነኛ ስራ በቅንጡው “Rolls Royce” መኪና መጥቶ የተነጠፈለት የክብር ቀይ ምንጣፍ ላይ እየተንጎማለለ መሄድ እና ብርቱካናማ ልብስ ያደረጉ ተከታዮቹን ወደ ማስተማርያ(ማምለኪያ) አዳራሽ ወስዶ እሱ እንደሚለው ማስተማር እና ማዳን ነው!
ያቺ 150 የማይሞሉ ሰዎች የሚኖሩባት ፀጥ ያለች ከተማ ወደ 30 ሺህ በሚጠጉ የ “Osho” ተከታዮች ተወረረች! ከተማዋ መረበሽ ጀመረች! “Osho” በሚያስተምርበት ወቅት ተከታዮቹ ይጮሃሉ፣ መሬት ላይ ይንደባለላሉ፣ እርቃናቸውን ይሮጣሉ፣ ሲፈልጋቸው ይደባደባሉ! የሚደብረው ደግሞ “ወሲብ ነፃ ነው!” በሚባለው ፍልስፍና ስለሚያምኑ በቡድን ሳይቀር ይዳራሉ።
ሴትየዋ አንድ ነገር ቀለሰች!
እነዚህ 150 የማይሞሉ ነዋሪዎችን ከከተማዋ አስወጥቶ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ የራሳቸው ነፃ ከተማ ማድረግ! ይህንን ደግሞ ማድረግ የሚቻለው ሃብት ንብረታቸውን በመግዛት ነበር! አልቀረም አደረጉት! ልብ በሉ የ “Osho” ተከታዮች በዛች ከተማ ብቻ ወደ 30 ሺህ ደርሰዋል! ነዋሪዎቹ ደግሞ ከ “150” አይበልጡም! በመጨረሻ ተከታዮቹ የህዝብ ድምፅ ብልጫውን ያዙ! ህጋዊ በሆነ መንገድም ምርጫ አድርገው “Antelope” የነበረውን የከተማዋን ስም “Rajneesh” እንዲሆን አደረጉ። እያንዳንዱን በከተማዋ የሚገኙ የመንገድ ስሞች ሳይቀር በራሳቸው መጠሪያ ቀየሩት! ምክር ቤቱን በአብላጫ ውክልና ያዙ! የዚህ ሁሉ “Mastermind” የ “Osho” ቃል አቀባይ፣ አፍቃሪው እና የግል ፀሃፊው “Sheela” ናት!
ታሪኩን ስናሳጥረው!
ይቺህ ሴት የ “Osho” ተከታዮች በመሰረቷት የአዲሲቷ ከተማ ባለቤትነት ምርጫ ወቅት የቀድሞ ነዋሪዎች ምርጫው ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ መርዝ አበላቻቸው፣ ከዛም አልፋ የግዛቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበረው ግለሰብ እንቅስቃሴዋን ይቃወም ስለነበር ልታስገድለው ሞክራ ሳይሳካላት ቀረ! “Osho”ም ሚድያ ላይ ቀርቦ ታሰልለው እንደነበር እና በተደጋጋሚ ልትገለው እንደሞከረች ከዛም አልፎ ብዙ ገንዘብ ዘርፋው እንደጠፋች ተናዘዘ።
በመጨረሻም!
“Sheela” ከጠፋችበት “Switzerland” ተይዛ የ “20 ዓመት” እስራት ተፈረደባት! “Osho”ም የአሜሪካን ምድር ድጋሚ እንዳይረግጥ ተወስኖ “Deport” ተደረገ! ሌሎች 21 ሃገራትም “ድርሽ እንዳትል!” ብለው በራቸውን ዘጉበት! ሃገርህ አትጥልህምና ወደተነሳባት ህንድ ተመልሶ ሄደ! በመጨረሻም እ.ኤ.አ 1990 ላይ በ 58 ዓመቱ በልብ ህመም ምክንያት እቺን ዓለም በሞት ተሰናበተ!
የሚገርመው!
“Sheela” የተፈረደባትን የ 20 ዓመት እስራት ሳትጨርስ በአመክሮ 3 ዓመት ብቻ ታስራ ወጣች!
አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ይህንን ትላለች!
“………”Osho” ጥሩ ልብ ያለው መልከ መልካም ሰው ነው! የተቻለኝን ሁሉ አድርጌ ለዚህ ክብር እና ዝና አብቅቼዋለው! የሱ ክፋት በሰዎች አዕምሮ እና ድክመት ላይ መጫወቱ ነው! የሱ ሃብትን መዝረፊያ መሳርያው “Meditation” ነው! ከተከታዮቹ እስከ 200 ሚልዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ዘርፏል! 98 ውድ ውድ የቅንጦት “Rolls Royce” መኪኖች አሉት! የሚያደርገው የዳይመንድ ሰዓቶችን ነው! በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ከአንድ ሚልዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያጠፋል! እሱ ማለት መኪና አዞ ወደቤቱ ሲመጣለት እንደ አጋጣሚ በግንባታ ምክንያት የተዘጋ መንገድ ያዘዘውን አዲስ መኪና ማሳለፍ ስላልቻለ 250 ሺህ ዶላር አውጥቶ አዲሱ መኪናውን ተሸክሞ የሚያሳልፍለት የጭነት መኪና የሚገዛ ሰው ነው! ጠጪ ነው፣ አደንዛዥ እፅ ይጠቀማል፣ እንቅልፍ መተኛት ስለማይችል ወደ ስልሳ ሚሊግራም የሚሆን መድሃኒት በየቀኑ ይወስድ ነበር! መጀመርያውኑ ወደ እርሱ የመጣሁት ፍልስፍናውን ወድጄው ሳይሆን ፍቅር ይዞኝ እና መልከ መልካምነቱ ስቦኝ ነው!…..”
ስናገባድድ!
“Sheela” አሁን ላይ 71 ዓመቷ ነው! በቅርቡ “Netflix” “Wild Wild country” የተሰኘ ስድስት ክፍል ያለው ዶክመንተሪ ሰርቶ ለዕይታ አቅርቧል! እሷም እዚህ ዶክመንተሪ ላይ ብዙ ያልተሰሙ ታሪኮችን ታጋራለች! ካገኘህ ሳትሰለች እየው! ታተርፍበታለህ!
ጠላህም ወደድክም “Osho” የ “20ኛው ክፍለ ዘመን” እጅግ አነጋጋሪ ሰው ነበር! ነገር ግን “Sheela” አነሳችው! “Sheela” ጣለችው!
መልካም ምሽት!
——
የፅሁፉ ባለቤት ፡ ጋዜጠኛ ወንድዬ እንግዳ