ኤድማፕ ፡ ስለ ራስሽ አንዳንድ ነገር ብትነግሪን?
ማህሌት ፡ ጋዜጠኝነት ላይ እሰራለሁ። ከዛ በተጨማሪ “ኮንተንት ክሬተር” ፣ “ዲጂታል ማርኬተር” ነኝ። በትርፍ ሰዓትም የኦንላይን ሾፒንግ ቢዝነስ ላይ እሳተፋለሁ።
ኤድማፕ ፡ የኦንላይን ሾፒንግ ቢዝነስ ላይ ለመግባት እና ለመጀመር ምን አነሳሳሽ? እንዴት እና መቼ ጀመርሽ?
ማህሌት ፡ ከ2 አመት በፊት Glossy Shopping የሚል የቴሌግራም ቻናል በመክፈት የኦንላይን ሾፒንግ ለመጀመር ከጓደኛዬ ጋር ተስማማን። ከዛም ገበያው አሪፍ ሲሆን እዚህ ስራ ላይ መቆየት እንዳለብኝና እንደሚያዋጣ ተረዳሁ።
ኤድማፕ ፡ አሁን ላይ የኦንላይን ሾፒንግ ቢዝነስ ለመጀመር ላሰበች ሴት ምን ትመክሪያታለሽ? ከየት ትጀምር? ምን ታድርግ?
ማህሌት ፡ በመጀመሪያ ምን ልሽጥ? ምን ብሸጥ ያዋጣኛል? ምን ስራ ከኔ ጋር ይሄዳል? ምን አይነት ኮኔክሽኖች አሉኝ የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።
በመቀጠል የቴሌግራም ቻናል ፣ የፌስቡክ አካውንት ፣ የኢንስታግራም አካውንትና ስራውን የምትሰሪበት የቲክቶክ አካውንት መክፈት አለባት። እነዚህን ካደረገች በኋላ የምትሸጣቸውን እቃዎች ፎቶ በመያዝ በከፈተቻቸው አካውንቶች በሙሉ መለጠፍ አለባት።
የቴሌግራም ቻናሏ ብዙ ሰው እንዲመለከተው እንደሷ የኦንላይን ስራ ከሚሰሩት ጋር “ክሮስ ፕሮሞሽን” ብታሰራ መልካም ነው።
ፌስቡክ ላይ ደግሞ ፌስቡክ ያዘጋጀው “Market Place” የተባለ ቦታ አለ እዛ ላይ ፎቶዎችንና ሌሎች ዝርዝሮችን መፖሰት ትጀምር። ኢንስታግራምና ቲክቶክ ላይ ግን በቪዲዮ እቃዎቿን ብታስተዋውቅ የተሻለ ነው።
ኤድማፕ ፡ የኦንላይን ሾፒንግ ቢዝነስ ለመጀመር ያሰበች ሴት መነሻ ገንዘብ ያስፈልጋታል?
ማህሌት ፡ ሁለት አይነት አማራጮች አሉ። የመጀመሪያውና እኔ የምመክረው እሷ ገንዘብ እንዳታወጣ ማለትም ያለመነሻ ገንዘብ እንድትሰራ ነው። ይሄ እንዴት ይሆናል ከተባለ Resell የሚባለውን ቴክኒክ በመጠቀም ነው። የሆነ ሱቅ ላይ በመሄድ “እኔ የኦንላይን ሾፒንግ ላይ እሰራለሁ እናም የእናንተን ዋጋ ንገሩኝ እና እኔ መሸጥ ልጀምር” ትላለች ከዛም እነሱ “እሺ” ሲሉ የእነሱ ዋጋ ላይ ጨምራ ለደንበኞቿ ትናገራለች። ደንበኞቿ ሲደውሉላት ወደ ሱቁ ትደውልና “የእኔ ደንበኞች እየመጡ ነው በእንደዚህ ዋጋ ሽጥላቸው” ትላለች። እቃው ሲወሰድ ወደ ሱቁ ሄዳ የጨመረቺውን ዋጋ ያክል ትቀበላለች ማለት ነው።
ሁለተኛው አማራጭ ፡ በትንሽ ገንዘብ የምትሸጣቸውን እቃዎች ገዝታ አትርፋ መሸጥ ነው።
ኤድማፕ ፡ ለስራሽ ምን አይነት የማርኬቲንግ ስትራቴጂ ትጠቀሚያለሽ? ደንበኞችንስ ከየት ነው የምታፈሪው?
ማህሌት ፡ እኔ የቴሌግራም ቻናሌ ላይ ደንበኞችን ያፈራሁት “ክሮስ” ፕሮሞሽን በመስራት ማለትም እኔም ልክ እንደኔ ተመሳሳይ ስራ ለሚሰሩ ሰዎች አስተዋውቃለሁ እነሱም ያስተዋውቁልኛል። ስለዚህም አዳዲስ ደንበኞችን እንዳገኝ ይረዳል። ፌስቡክ ላይ ደግሞ የፌስቡክ ማርኬት ፕሌስ በመጠቀም የምሸጣቸውን እዛ ላይ አስተዋውቃለሁ፣ የተለያዩ ለግብይት የሚጠቅሙ አፕሊኬሽኖች እና ድህረገፆችም እንደ Qefira የመሳሰሉት ደንበኞችን እንዳፈራ አድርገውልኛል። ያው ኢንስታግራም እና ቲክቶክ ላይ ማስተዋወቁ ሳይረሳ ማለት ነው።
ኤድማፕ ፡ አንቺ የተለያዩ የቢዝነስ ስራዎች ላይ ትሳተፊያለሽ… ለአብነት ያክል ልብሶች፣ ጫማዎች፣ ሽቶዎች ወዘተ ስትሸጪ አይተናል። የትኛው አዋጭ ነው?
ማህሌት ፡ አዎ በተጨማሪም ሰዓቶችና ቦርሳዎችንም እሸጣለሁ። ግን የትኛው ያዋጣል ለሚለው እንደከስተመሮቻችሁ ይወሰናል። ከስተመሮቼ ምን ይፈልጋሉ የሚለውን ለማወቅ ደግሞ ሁሉንም አይነት እቃ በማስተዋወቅ መሞከር ይቻላል። ከዛም ብዙ የተጠየቀውና ሰው ሊወስድ የፈለገው ያ ምርት ለእናንተ የሚያዋጣ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ያንን ምርት ብቻ ወደ መሸጥ ትመጣላችሁ ማለት ነው።
ኤድማፕ ፡ የትኛው ማህበራዊ ሚዲያ (Social Media) ለስራው ይበልጥ አሪፍ ናቸው?
ማህሌት ፡ ቲክቶክ እና ፌስቡክ ማርኬት ፕሌስ አሪፍ ነው ለኔ። ለሌሎች ደግሞ ቴሌግራም እና ኢንስታግራም ብዙ ደንበኞች ያገኙበታል። እንደ ከስተመር አይነት ነው።
ኤድማፕ ፡ በኦንላይን ሾፒንግ ቢዝነስ ላይ ያጋጠመሽ ችግር አለ? ካለስ እነሱን ችግሮች እንዴት ማለፍ ቻልሽ?
ማህሌት ፡ አዎ፣ አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ለምሳሌ “ከስተመር” ሀሳቡን ሊቀይር ይችላል ፣ የ”ዴሊቨሪ” ቦታ በትክክል ላያሳውቁ ይችላሉ፣ የጊዘ መባከን እና የመሳሰሉት ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ለዚህም እንደ መፍትሄ ብዬ የማስበው አስቀድሞ ግልፅ መረጃ መነጋገር፣ የታወቀ ቦታ ለ”ዴሊቨሪ” መምረጥ ነው።
ኤድማፕ ፡ ከደንበኞችሽ ቅሬታ ሲመጣ እንዴት ነው የምታስተናግጂው?
ማህሌት ፡ ቅሬታ ሊመጣ ይችላል። ነገር ግን ይቅርታ በመጠየቅ እና እቃዎቹ መተካተ የሚቻሉ ከሆነ በመቀየር ችግሩን መፍታት ይቻላል።
ኤድማፕ ፡ ከዚህ የኦንላይን ሾፒንግ ቢዝነስ የተማርሺው ትልቁ ትምህርት ምንድን ነው?
ማህሌት ፡ ከስተመር ከምንም ነገር ይበልጣል፣ የነሱን ፍላጎት ማክበር ለነገ ቢዝነስ ትልቅ አስታዋፆ እንዳለው መረሳት የለበትም። ፌር ያልሆነ ነገር ቢገጥማት እንኳ እሷ ብትጎዳ ይሻላል ምክንያቱም ደንበኞቿ ወደፊት እንዲበዙ ያደርጋል። ስራው ሰውን እንዳከብር ፣ ትዕግስት እንዲኖረኝ እንዲሁም ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት እንድፈጥር አግዞኛል።
ኤድማፕ ፡ ለሴት ተማሪዎች እና ይሄን ስራ ለመስራት ለሚፈልጉ በሙሉ ምን ትመክሪያቸዋለሽ?
ማህሌት ፡ እንዲሰሩ አበረታታለሁ። ምክንያቱም በጣም ቀላል ነገር ግን አዋጭ ስራ ነው። የግድም በቦታው መገኘት አይጠበቅባቸውም ፤ ባሉበት ቦታ ሆነው መስራት ይችላሉ። መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው አካባቢያቸው ላይ ያለ ባለሱቅ ጋር በመሄድ ማነጋገር በይበልጥ ደሞ የኦንላይን ገበያ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሱቆችን ማዋራቱ የተሻለ ነው። ከዛም የእነሱን እቃዎች እናንተ ገፅ ላይ ማስተዋወቅ እና ሰዎች ሲደውሉላችሁ ወደ ሱቁ መላክ ይሆናል የእናንተ ስራ። ለደንበኞቻችሁ ዋጋ ስትናገሩ ከባለሱቁ ተመጣጣኝ የዋጋ ጭማሬ ማድረጋችሁን አትርሱ – ገበያችሁ ያ ነውና!
ኤድማፕ ፡ ካንቺ ጋር መስራት የምትፈልግ ሴት እንዲሁም ካንቺ እቃ መግዛት የሚፈልጉ የት ሊያገኙሽ ይችላሉ?
ማህሌት ፡ በሁሉም ሶሻል ሚዲያዎች አለሁ። ቴሌግራም ላይ @glossythrift ብለው ሰርች ቢያደርጉ የኔ ቻናል ይመጣላችኋል።
ኤድማፕ መሰል እናንተ በትርፍ ሰዓታችሁም ሆነ በሙሉ ጊዚኢያችሁ እየሰራችሁ ገንዘብ የምታመጡባቸውን መንገዶች ከመጠቆም ባሻገር እንዴት እንዴት እንደምታስኬዷቸውም ለእናንተ ማሳወቁን ይቀጥላል።