ኤድማፕ : ስለ ራስሽ አንዳንድ ነገር ብትነግሪን?
ሃፊ : ሃፍሳ ሰለሞን ወይም ሀፊ ትንሿ ዲዛይነር በመባል እታወቃለሁ። የህፃናት እና የአዋቂ ልብሶችን ዲዛይን አደርጋለሁ፣ እሸጣለሁ።
ኤድማፕ ፡ የፋሽን ዲዛይነር ለመሆን መቼ አሰብሽ? ከዛም መቼ ጀመርሽ?
ሃፊ ፡ ዲዛይነር የመሆን አልነበረኝም ነበር። ግን ኮሮና በሽታ በተንሰራፋበት እና ከቤት መውጣት ግድ በሆነበት ጊዜ አዘውትሬ የቱርክ ፊልም ማየት ጀመርኩ። ፊልሞቹ ላይ ሳያቸው የነበሩ አልባሳትም ፋሽን ዲዛይነር እንድሆን ገፋፉኝ። በትክክል ወደ ስራ እንደ ሀፊ ዲዛይን የገባነውም ህዳር 27/2014 ዓ.ም ላይ ነው።
ኤድማፕ ፡ ስራዎችሽን የመሥራት ችሎታ እንዴት አዳበርሽ? ምን ዓይነት ዘዴዎችን ተጠቀምሽ?
ሃፊ ፡ ስራዎቼን ያዳበርኩት ዩቲዩብ ላይ ነው። ዩቲዩብ ላይ በልብስ ዲዛይን ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ ቪዲዮች መመልከት ጀመርኩ። ዲዛይን ማድረግ፣ ፓተርን ማውጣት እና ሌሎች መሰል ለልብስ ዲዛይነር የሚጠቅሙ ስራዎችን ራሴን በራሴ በዩቲዩብ እያስተማርኩ ነበር። ዩቲዩብ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው ለኔ። ራሴን በቪዲዮዎቹ በመታገዝ አሪፍ ልምድ ካስገኘሁት በኋላ ወደ ዲዛኒንግ ትምህርት ቤት ገባሁ።
ኤድማፕ ፡ አሁን ላይ የፋሽን ዲዛይን ስራ ለመጀመር ላሰበች ሴት ምን ትመክሪያታለሽ? ከየት ትጀምር? ምን ታድርግ? ቅደም ተከተሉን ንገሪን።
ሃፊ ፡ ከራሷ እና ከቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ትጀምር። ከዩቲዩብ የተማረቺውን እውቀት እና ልምድ በመጠቀም ያረጁ እና የተቀደዱ ልብሶችን ወደ ሌላ ዲዛይን ለመለወጥ መሞከር አለባት። በዚህ መንገድ የተወሰነ ያክል እጇን ካፍታታች በኋላ ፓተርን እያወጣች እና ጨርቆችን እየገዛች ስራዎን እያዳበረች መምጣት ትችላላች። ስለዚህ አሁን መጀመር ከፈለጋችሁ ትምህርትቤት ከመግባታችሁ በፊት ራሳችሁን በዩቲዩብ አስተምሩ። ምክያቱም ትምህርት ቤት ውስጥ የምታገኙት ትምህርት “ቤዚክ” የሚባለውን ነው።
ኤድማፕ ፡ አንዲት ሴት ይሄን ስራ በምትጀምርበት ጊዜ የሚያጋጥሟትን የአቅርቦት ፈተናዎች እንዴት ማለፍ ትችላለች? ለምሳሌ የጨርቅ እና የማሽን አቅርቦት እጥረት ካለባት እንዴት ማለፍ ትችላለች?
ሃፊ ፡ ጀማሪ ከሆነች ማሽኑ አያስፈልጋትም። ከላይ እንዳልኩት እጇን ለማፍታታት እና ስለስራው ትንሽ እውቀት እንዲኖራት በመርፌ እና በክር እየታገዘች በእጇ መስራት ትጀምር። ከዛም ፓተርን ወደ ማውጣት እንዲሁም አዲስ ዲዛይን ወደ መስራት ያደገች መስሎ ሲሰማት ዲዛይኗን ይዛ ወደ ልብስ ሰፊዎች በመሄድ ማሰራት። እንዲህ እያለች ስራዎቿን ማዳበር። ከዛም ብቁ ስትሆንና አሪፍ ሽያጭ ሲኖራት የልብስ ማሽኑን በመግዛት ስራዋን አጠናክር መቀጠል ። የጨርቅ አቅርቦት በተመለከተ ለመለማመድ ከሆነ ብዙ በማይፈለጉ ጨርቆች መለማመድ፣ ወደ መሸጡ የሚያደርስ ችሎታ ላይ ነኝ ብላ ካሰበች ደግሞ ቀብድ በመቀበል ከዛም በዛ ጨርቁን መግዛት ትችላለች።
ኤድማፕ ፡ በዚህ ሙያ ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? እነዚህን ፈተናወችሽ እንዴት ማለፍ ይቻላል?
ሃፊ ፡ ብዙ ፈተናዎች እና ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያክል “የሰራነው ስራ እንደምንፈልገው ላይመጣልን ይችላል ፣ ከስተመር እንደሚፈልገው ላንሰራ እንችላለን ፣ ቦታዎችን ባለማወቃችን ብቻ ለምንሰራው ስራ የሚያስፈልገንን ጨርቅ በውድ ልንገዛ እንችላለን…” ሌሎች ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። የሰራነው ስራ እንደምንፈልገው ካልመጣ የምንፈልገው ድረስ በተደጋጋሚ መስራት ፣ ከስተመር የማይፈልገው ከሆነም በማስተካከል እንዲሁም ጨርቆችን የምንገዛበት ቦታም በማጠያየቅ የሚያግጥሙን ችግሮች ወደ መፍትሄ መለወጥ እንችላለን።
ኤድማፕ ፡ እዚህ ስራ ውስጥ መግባት ለሚፈልጉ ሰዎች ምን ትመክሪያቸዋለሽ?
ሃፊ ፡ እዚህ ስራ ውስጥ መግባት እየፈለጉ ግን ገብተው ለመስራት የማይደፍሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ምክንያቱ ደግሞ ፍርሃት ነው። ጀማሪ በምትሆኑበት ሰዓት ፍራቻ ይኖራል። ፍራቻው ደግሞ ባልሰራውስ፣ ብሳሳትስ የሚል ነው። ታላላቅ ዲዛይነሮች ራሱ ሲሰሩ ይሳሳታሉ ፤ መሳሳት ችግር የለውም ። ከስህተት ወዲያው መማር እና ደፈር ብሎ ፍላጎትን ማሳካት አለብን። ስለዚህ ፍላጎታችሁ ከሆነ ስሩ።
ኤድማፕ ፡ ምርቶችሽን በኦንላይን እንዴት ነው ለህዝቡ የምታቀርቢው? ብዙ ደንበኞችሽ የሚመጡት በኦንላይን ነው ወይስ ከኦንላይን ውጪ?
ሃፊ ፡ ብዙ ደንበኞቼ የሚመጡት በኦንላይን ነው። ስራዎቼን ቲክቶክ፣ ኢንስታግራምና ቴሌግራም ላይ አስተዋውቃለሁ። በይበልጥ ቲክቶክ ላይ የምለቃቸውን የስራዬ ውጤቶች ተመልክተው ብዙ ደንበኞቼ ሊያሰሩ ይመጣሉ።
ኤድማፕ ፡ ይህ የፋሽን ዲዛይን ቢዝነስ አዋጭ ነው?
ሃፊ ፡ በደንብ ከያዝነው እጅግ በጣም አዋጭ ነው።
ኤድማፕ ፡ ሀፊ ዲዛይን ከአመታት በኋላ የት እንጠብቀው?
ሃፊ ፡ ኢንሻላህ ፣ በጥቂት ጊዚያት ውስጥ ብዙ ቅርንጭፎች ይኖሩናል። የራሴን የልብስ ብራንድም ለመጀመር አስቢያለሁ።
ኤድማፕ ፡ ካንቺ ልብስ ማሰራትና መግዛት የሚፈልጉ የት ሊያገኙሽ ይችላሉ?
ሃፊ ፡ አድራሻችን አዲስአበባ ፣ አየርጤና ጅማበር ፖሊስ ጣቢያ (ወደ ጀሞ መውረጃ) ዝቅ ብሎ ካለው ህንፃ 2ኛ ፎቅ ላይ ወይም ደግሞ በ 09-65-18-02-52 ይደውሉልን። ቴሌግራም ቻናላችንን @hafi_collection ብለው ያገኙታል።