እኛ የምርጫዎቻችን ውጤት ነን ” ፤ ግራ ያጋባል አይደል? ላብራራልህ። በየዕለቱ በየደቂቃው ህይወታችን በምርጫ ላይ የተወሰነ ነው። ትልቅ ሊሆን ይችላል ፤ ትንሽም ሊሆን ይችላል። ኧረእንደውም ከናካቴው እርባና ቢስም ሊሆን ይችላል። ትንሽ ስልህ ምን ማለቴ ነው? “የትኛውን የቲቪ ቻናል ልመልከት? ያኛውን ወይስ ይሄኛውን” ወይም ደግሞ “የተላከልኝን ቴክስት ልመልስ ወይስ ልተወው?” እስከማለት የደረሰ ነው። ትላልቅ ምርጫዎች ደግሞ አሉ “ማግባት አለብኝ እንዴ?” “አዲስ የምጀምረው ቢዝነስ ላይ ጊዜዬን እና ገንዘቤን በደንብ ላውጣ” ወዘተ የሚሉ። በህይወት መንገድ ላይ እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ሀሳብ ይዞ ይኳትናል። ሀሳቡ “ውሳኔ” ወልዶ ወደፊት በሚራመድባቸው እርምጃዎች ላይ ኮቴውን ማሳረፉ አይቀርም። ለአብዛኛው ሰው የመጀመሪያውና ለቀጣዩ እርምጃዬ ጉልህ ሚና አለው ብሎ የሚያስበው ውሳኔ የሚሆነው የሚማርበትን ዩንቨርስቲ ወይም ኮሌጅ መምረጥ ነው።በሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙሃኑ የተማሪዎች ጉዞ ይሄን ይመስላል። የአንተም ይሄንን እንደሚመስል እርግጠኛ ነኝ።ሀይስኩል መግባት፤ሁሉንም የትምህርት አይነቶች በጥሩ ውጤት ተምሮ ማጠናቀቅ፤የዩንቨርስቲ የመግቢያ ፈተናን ማለፍ ከዛም ሜዲሲን ወይም ኢንጅነሪንግ መግባት እና ተሳሳትኩ?ይሄ ጉዞ ለረጅም ጊዜያት ተለምዷል።
ለምን???? ግን ለምን??????
በህክምና (Medicine) እና ምህንድስና (Engineering) የትምህርት ዘርፎች ላይ የማህበረሰቡ በተለይም የቤተሰብ፣ የወዳጅ ዘመድ፣ የጓረቤት፣ የጓደኛም ብሎ የመምህራን የተጋነነና ከተጨባጭ እውነታ ያፈነገጠ ነው።በህብረተሰባችን እነዚህ የትምህርት ዘርፎች ብቻ ወርቃማ ሌሎቹ ደግሞ እምብዛም ናቸው ተብለው ይታያሉ። ለዛም ከዚህ አስተሳሰብ ላለመውጣት በሚል ፍርሃት ብቻ ተማሪዎች ከላይ ለጠቀስኩት አዙሪት ራሳቸው አሳልፈው ይሰጣሉ። በተጨማሪ ተማሪዎች በሀይስኩል የትምህርት ወቅታቸው ከትምህርታቸው ውጪ ያለውን ህይወት እንዲያዩ እና ያሉትን የስራ አማራጮች እንዲመለከቱ አለመደረጋቸው ትልቅ ጥፋት አምጥቷል። ኢንተርንሽፕ ፣ የበጓ አድራጎት ስራዎች እና ጎን ለጎን የሚሰሩ ስራዎች የተማሪዎችን አዕምሮ በተስዕጦ እና በችሎታ እንዲዳብር ያደርጋሉ።
ወዳጄ፣ እኔ በምን አምናለሁ መሰለህ!? “የማይሆን እና ከባድ ነገር መሞከር ምንም ካለመሞከር ይሻላል” የሆነ ነገር አለመቻልህን ማወቅ ያን ነገር እችለዋለሁ ወይስ አልችለውም እያሉ ከመወዛገብ አያድንምን? ነገርግን ተማሪዎች ይሄንን ሀሳብ በመፍራት በዩንቨርስቲዎች እና ኮሌጆች ላይ የሚሰጡ ሌሎች ዘርፎች ሳያስተውሉ ይታያሉ።አንድ ተማሪ አስተዋይ አይን እና የስዕል ችሎታ እንዳለው ካላወቀ እንዴት የውስጥ ንድፍ ባለሙያ (Interior Designer) እና የስነህንፃ ባለሙያ (Architecture) መሆን ይችላል?
እርግጥ ነው፣ በሀገሪቱ የገጠራማ ክፍል የሚኖሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች አዳዲስ ለሚመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና መሰረተ ልማቶች ቅርብ ለመሆን ያዳግታቸዋል። ይሄንንም ተከትሎ ከቴክኖሎጂው ጀርባ ያሉት ድንቅ ነገሮች ላይ እምብዛም ትኩረት ባያደርጉ አያስገርምም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ስለጀመረችው የ5G ኔትወርክና በአዲሱ የቴክኖሎጂ ሙዚየማችን ላይ ስለታየው ቨርችዋል ሪያሊቲም ያን ያህል ላይደንቃቸው ይችላል።ከዛ ይበልጥ በአካባቢያቸው ያለ በብቁ የህክምና መሳሪያዎች ያልታገዘ ሆስፒታል እና ከቤት ወደ ትምህርትቤት የሚወስዳቸው ረጅምና አሰልቺው ኮረኮንቻማ መንገድ ላይ ሀሳባቸው ሊሰረቅ ይችላል። ለነሱ ይሄ ምርጫ አይደለም ይልቁንም ለማህበረሰቡ የተሻለ የጤና ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ፣ ለህፃናትና ለተማሪዎች ደግሞ ወደ ትምህርትቤት የሚወስዳቸውን ምቹ መንገድ መስራት ሀሳብ እና ህልም ብሎም ተልዕኮ ነው። “የምንኖረውን ነው የምንመስለው” ይባል አይደል!? ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አካባቢያችን ለምንወስናቸው ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የታወቀ ነው።
ዩንቨርስቲ ከተገባ በኋላ ቀጣይስ ምን ይፈጠራል? በሁሉም ዘንድ ምህንድስና (Engineering) እና የህክምና (Medicine) ትምህርት አቅምን የሚፈትሽ እንደሆነ ይታሰባል። ከትምህርቱ ጋር ስለሚመጣው አዕምሮ አስጨናቂነት ተፅዕኖ ግን ማንም ሲናገር አይታይም። እነዚህ ዘርፎች እጅግ አሰልቺ እና ረዘም ያለ ጊዜን የሚወስድ ጥናት እና ስራ ይፈልጋሉ። ተማሪዎችን ጭንቀት እንዲሰማቸው ከማድረጋቸው በተጨማሪ የመዛል ስሜት እንዲያድርባቸው እና ድባቴ ውስጥ የተዘፈቁ ያክል እንዲሰማቸው ለማድረግ አይቦዝኑም። ይሄም ጊዜያቸው እያቃጠሉ እና ብኩን ህይወት እየመሩ እንዳለ እንዲሰማቸው ያደርጋል። የሚያመጡት ውጤት ደግሞ ከሀይስኩል ውጤት ጋር ሲተያይ እንደ ገለባ ይቀልባቸዋል። በውሳኔያቸው መፀፀት እና ለነዚህ የትምህርት ዘርፍ እንደማይገቡ ማሰብ ተከታዩ ነገር ይሆናል።
አብዛኛው ሰው እያቋረጠ ከፊሉም ጥርሱን ነክሶ ሲመረቅ ይታያል። 5 እና 7 አመታት የማይፈልጉትን ትምህርት መማር ከባድ መሆኑ አያጠያይቅም። ተመርቆ ወጥቶ ደግሞ ቀጣይ ለአመታት እና እስከ ህይወት ፍፃሜ በዛው ዘርፍ ተወስኖ መስራትን ማሰብ ደግሞ ይበልጡኑ ከባድ ያደርገዋል። በየአመቱ በነዚህ የትምህርት ዘርፎች የሚመረቁ ተማሪዎች መብዛት የቀጣሪ–ተቀጣሪን መጠን እንዲጥሱና ያለመቀጠር መረብ ውስጥ እንዲታሰሩ እያደረገ መሆኑ በግልፅ ይስተዋላል።
ተፅዕኖው ይቀጥላል። ድባቴ ወይም ድብርት አንድ ግለሰብን ብቻ አያጠቃም። ይዛመታል። ወደቤተሰብ ይገባል። ይዋረሳል። ወላጅ አሳዳጊዎች በደለኛ እንደሆኑ ያስባሉ፣ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ራሳቸውን ይወቅሳሉ። ልጃቸው ወይም ተማሪው በመሃል ትምህርቱን አቋርጦ ሌላ ዘርፍ ለመማር ቢወስን ደግሞ ሌላ የኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይሆናል። ሀገር የቤተሰብ ድምር ነች። የተጎዳ ቤተሰብ የተጎዳ ሀገር ይፈጥራል። በዚህ ጊዜ መጥፎ የስራ ባህሪያት ያላቸው ግለሰቦችን የሚታዩት በሚሰሩት ስራ ባለመደሰታቸው እና ባለመርካታቸው ነው። ስለዚህ ምን መደረግ አለበት? መልካም።
የመጀመሪያው እና ፈር ቀዳጁ ሌሎችም የትምህርት ዘርፎች እንደ ምህንድስና /Engineering/ እና ህክምና /Medicine/ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ እያሳወቁ ማህበረሰቡን ማንቃት መሆን አለበት። በይበልጥ ደግሞ በሀይስኩል የትምህርት ወቅት ላይ የተለያዩ የትምህርት ቤት ክበባትን በማቋቋም ተግባር ተግባር ነክ የመማር ማስተማር ሂደቶች ቢኖሩ ይበል የሚያሰኝ ለውጥ እንደሚኖር እሙን ነው። ከዚህ በፊትም እንደተገለፀው ኢንተርንሽፕ፣ የበጎ አድራጎት ስራዎች እና የጎን ለጎን ስራዎች ከትምህርታቸው በተጨማሪ ወሳኝ የህይወት ክፍሎች እንደሆኑ ማስገንዘብ አለብን። ሌላው በሀይስኩል ጊዜያት በተማሪዎች የወደፊት የስራ መስክ ምርጫ ላይ እገዛ ቢፈጠር መልካምነቱ የጎላ ነው።
በዚህ ትውልዱ በዲጂታላይድ መድረክ አንድ በሆነበት ዘመን፣ የአለማችን የእያንዳንዷ እንቅስቃሴ በመዳፋችን ስር ወድቋል ቢባል ሀቅ ነው። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስተር (MOSHE) እንዲሁም በሀገሪቷ የሚገኙ ዩንቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች የታደሰ እና አዲስ የዲጅታል መሰረተ ልማት ቢኖራቸው፣ በውስጣቸው አቅፈው የያዟቸውን የትምህርት ዘርፎች ላይ በቂ መረጃዎች ቢያቀርቡ፣ በየአመቱ ምን ያክል ተማሪዎች ሊቀበሉና ሊያስተምሩ እንዳቀዱ፣ ተማሪዎቻቸው እየሰሩ ያሉትን ወይም ሰርተው ያለፉትን ፕሮጀክቶች ቢያሳውቁ ምን ያክል ለተማሪዎች ቀላል እና መልካም እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። እንደነዚህ አይነት ድህረገፆች ቢኖሩ ያልተገደበ እገዛ እንደሚያደርጉ ያስታውቃል። ከታች የተዘረዘሩትን ዘርፎች ተመልከቱ።
1) ኮምፒውተር ሳይንስ
ኮምፒውተር ሳይንስ የተለያዩ ውስብስባዊ ችግሮችን ቴክኒካዊ መንገዶችን በመጠቀም የመፍታት ሂደት ነው። በኢኮኖሚው፣ በኢንዱስትሪው እንዲሁም በዘመናዊ ኢኮኖሚ በሚሰሩ ድርጅቶች ውስጥ ኮምፒውተር እና ቴክኖሎጂን በማዋህድ የተቀላጠፈ አሰራር መዘርጋቱ እጅግ ጠቃሚ የትምህርት መስክ መሆኑን ያሳያል። ዘመናዊ የንግድ ስርዓት እና ኮምፒውተር መር ቴክኖሎጂን ለየቅል ላስኪድ ማለት እብደት ነው። ለዛም ሰዎች ኮምፒውተር ሳይንስ እጅግ ብዙ ጥቅም አለው ሲሉ የሚስተዋሉት።
2) ባዮ ቴክኖሎጂ
ባዮቴክኖሎጂ በአካባቢ፣ በፋርማሲዮቲካል እንዲሁም በግብርና ኢንዱስትሪዎች ላይ ህያዋን ሴሎች ያላቸው ጠቀሜታ ላይ ይንተራሳል። ለዚህ ዘመን በሳይንስና በቴክኖሎጂ መስክ አዳዲስ እይታዎችን ለመፈተሽ እድል የሚሰጥ ሁለንተናዊ የትምህርት ዘርፍ መሆኑ ይበል ያሰኛል። በተጨማሪዎ ይህ ብቅ ብቅ እያለ የመጣው የትምህርት መስክ ከምርምር እስከ ልማት ፣ ከሽያጭ እና ግብይት እስከ የጥራት ቁጥጥር እና ማረጋገጫ ድረስ በርካታ የሙያ እድሎችን ይሰጣል። በባዮቴክኖሎጂ በተሳካ ሁኔታ የተመረቁ ተማሪዎች እንደ ምግብ እና መጠጥ ኢንዱስትሪ፣ ጨርቃጨርቅ
ኢንዱስትሪ እና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ወዘተ ባሉ መስኮች ተስፋ ሰጪ የስራ መደቦችን መፈለግ ይችላሉ።
3) ባዮ ኬሚስትሪ
የዲግሪ የኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ መርሃግብር በዘርፉ የሚኖሩ ተመራማሪዎችን ለመፍጠርና ብሎም አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የተነደፈ አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው። ፖሊመር ሳይንስ፣ ሰርፋክታንት ኬምስትሪ፣ ሪያክሽን ኢንጅነሪንግ ፣ ፕሮሰስ ኢንጅነሪግ እና ኮምፒዩቲሽናል ኢንጅነሪንግ ፤ ተማሪዎች ሳይንስን በመቀመር መፍትሄ እንዲሰጡ የተዘጋጁ የትምህርት አይነቶች ናቸው። በመርሃግብሩም ተማሪዎች የተለያዩ ቴክኒካዊ ነገሮችን በመማር ለፊዚዎኬሚካል ባህርያት ቀመር እንዲያወጡላቸው ይደረጋል።
4) ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ
ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ በፊዚካል ሲስተም፣ በዲቨሎፕመንት ዲዛይን፣ በቴስቲንግ፣ በዲፕሎይመንት፣ ሶፍትዌሮችን በማዘጋጀትና በመሰደር ረገድ ላይ የሚሰማራ የትምህርት ዘርፍ ነው። በመላው አለም ላይ ያሉት ሶፍትዌሮች ለመጎልበት፣ ለመጠገን እና ለመታደስ በሚሹ ጊዜ የሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ትምህርት ያካበተ ተማሪ መፈለጉ አይቀሬ ነው። ይህም የሶፍትዌር ኢንጅነር የወደፊት የስራ መስክ እያደገ መሄዱ አይቀሬ እንደሆነ ያሳያል።
ማጣቀሻ
1. https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles
2. https://csuglobal.edu/blog/why-computer-science-so-important
3. Biotechnology: A Popular Career Choice | Shoolini University
I am a 4th year Bsc Mathematics student of University of Gondar and they are saying that PGDT is required to be employed as a high school teacher. And what does the new education system say about this? In addition, there is something called elementary school teachers with a first degree. When will this start?