የፋሽን እና ንድፍ ጉዞው ጅማሬ
አማኑኤል የስነጥበብ /Art/ ፣ የውስጥ ንድፍ ዲዛይንና /Interior design/ ፣ የኪነህንፃ /Architecture/ ፍላጎቱን ወደ ጎን የተወው ፤ የዩሃንስ ጎይቶም፣ የማፊ እና የአና የዲዛይን ስራዎች በተመለከተ ጊዜ ነበር። ለፋሽን ያላቸውን የተለየ መነሳሳት ሲያስተውል እሱም የራሱን ሀሳቦች በፋሽን ላይ ማንፀባረቅ እንዳለበት ተሰማው። ለፋሽን በቀረበ ቤተሰብ ውስጥ ማደጉ በተለይም ወላጅ እናቱ የልብስ ስፌት እደ ጥበብ የሚያስተምሩ ሆነው መገኘታቸው ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲገባ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ያምናል። ፋሽን ዲዛይን ጨርቆችን በመጠቀም የራሳችንን ልዩ ቀለሞች እና ቅርጾች መፍጠር የምንችለበት ጥበባዊ መንገድ እንደሆነ ሲገነዘብ በፋሽን ዲዛይን ፍቅር ለመውደቅ አላቅማማም።
ጓደኞቹ ከሚለብሳቸው ልብሶች በመነሳት ሞዴል እንደሚመስል እየነገሩት ቢቆዩም እዚህ ድረስ ፍቅሩ እንዳለው ግን አልጠበቁም ነበር። ቤተሰቦቹም በፋሽን ዲዛይን ውስጥ ሊያሳርፍ ባሰበው አሻራ ላይ ውሳኔውን በማክበር እንዳበረታቱት ይናገራል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደሚያስበው ዩንቨርስቲ ውስጥ ሲገባ የህክምና ትምህርት /Medicine/ እና ምህንድስና /Engineering/ ለመማር አልፈለገም ይልቁንም ወደ ጥበባት እና ፈጠራ በተለይም የፋሽን ዲዛይን ፍላጎቱን በማስቀደም በነዚህ ላይ ለመማር ወሰነ። የክት እና የባህላዊ የኢትዮጵያ ልብሶች በህዝቡ መወደድ ፤ የተዘነጉ የፋሽን ጊዜያት እንዳዲስ ማስተዋወቁ እና ለማህበረሰቡ ተዳራሽ ማድረጉ እውቅናና ስም እንደሚያስገኘው እርግጠኛ ነው።
የዩንቨርስቲ ቆይታ
የውስጥ ንድፍ /Interior design/ ወይም ስነህንፃ /Architecture/ መማር ያቅድ የነበረው አማኑኤል አዲስአበባ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ምርጫው ነበር። ነገርግን ሁለተኛው ምርጫ የሆነው ባህርዳር ዩንቨርስቲ እንደተመደበ ባወቀበት ጊዜ እቅዶቹን ወደጎን በመተው ፍላጎትና ህልሙን ለማሳካት ጥበባዊ ትምህርቶችን ለመማር ወሰነ። ቅድመ ምህንድስና /Pre-Engineering/ እና ቅድመ ማስገንዘቢያ ትምህርቶች /Common course/ ከወሰደ በኋላ የፋሽን ዲዛይን ትምህርቱን ሀ ብሎ ጀመረ።
መሰናከልን መወጣት
እንደ አብዛኛው የዩንቨርስቲ ተማሪ አማኑኤል በቆይታው ብዙ ችግርና መሰናክሎች ውስጥ ለማለፍ ተገዷል። ትልቁና ከባዱ መሰናክል ብሎ የሚገልፀው ግን እሱና ጓደኞቹ በተለያዩ ግለሰቦች ይደርስባቸው የነበረው የጥላቻና መረን–ቢስ ወቀሳ ነበር። ነገር ግን ይሄ ወቀሳ እሱ ላይ ተፅዕኖ እንዲያመጣበት አልፈቀደም ይበልጥኑ ወደፊት እንዲራመድ እና ህልሞቹን ማሰብ እንዲጀምር አደረጉት እንጂ።
“ፀሎት..” ይላል አማኑኤል። “ፀሎት አዕምሯዊ ሰላም ለማምጣት የምንሄድበት መንገድ ነው።” መፀሀፍት እውቀትና ተነሳሺነት እንደሚፈጥሩለትና ለህይወቱ ምቹ ሆኖ እንዳገኛቸውም ይናገራል። “ይሄ የትምህርት መስክ ተሞክሮ–ነክ (Practical) እና ፈጠራዊ መንገዶችን የሚያስተምር እንጂ እንደሌሎቹ የትምህርት አይነቶች በፅንሰ–ሀሳብ (Theory) ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም። ይሄንን ትምህርት ለመውሰድ ራስን መሆን፣ እና በራስ ምርጫ ሀላፊነት መውሰድን ይፈልጋል።“
“ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አነቃቂ ነገር ከመፈለግ መጀመሪያ ወደ ውጪ ወጥቶ አካባቢን መቃኘት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጥቂት ያየናት ነገር በኛ ላይ ተነሳሺነት እንዲፈጠር የማድረግ አቅሙ ይኖራታል። ከዛም የራስን ፈጠራ በመጠቀም ስራን መስራት ፤ በምንም መልኩ ቢሆን በዙሪያው ካሉ ለሚመጣ ምላሽና አስተያየት ጆሮን አዘጋጅቶ መጠበቅ አስፈላጊ ነው።“
“እንደ ህፃን ብናልም ለታላቅነትና ለትልቅነት እንሰራለን … ታላቅም እንሆናለን !”
@amnu.atle (Amanuel Atle)
Written by: Hanna. F